ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት 2014

መስከረም 14 ቀን 2014 - የኢመየብማ ባልደረባ

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማኅበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ63ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም መስማት የተሳናቸው ሕዝብ ሳምንትን በደማቅ ሁኔታ አከበረ፡፡ åበዓሉ ዓርብ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. መስማት የተሳናቸውና
ከተለያዩ አጋር ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉደይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ምክትል ኃላፊ 
         አቶ ሲሳይ ጥላሁን ለታዳሚዎች ንግግር ሲያደርጉ

በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉደይ ሚኒስቴር
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ምክትል ኃላፊ
አቶ ሲሳይ ጥላሁን ለታዳሚዎች ንግግር ሲያደርጉ
(ፎቶ፡ ጳውሎስ ካሡ፣ ዶ/ር)

በበዓሉ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጳውሎስ ካሡ (ዶ/ር) ‹‹በመበልጸግ ላይ ያሉትን የመስማት የተሳናቸው ማኅበረሰቦች እናክብር!›› የሚለው የዓመቱ መሪ ቃል ተገቢ መሆኑን ገልጸው መሪ ቃሉ መስማት የተሳናቸው በአካል ጉዳተኝነት ብቻ ከመፈረጅ አልፈው ለቋንቋቸው፣ ለባህላቸውና ለታሪካቸው እውቅና ያገኙበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡ መስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያንም ገና ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ቀደም ካሉት ጊዚያት ጋር ሲነጻጸር በቋንቋ፣ በባሕል፣ በታሪክ፣ በመብትና በኢኮኖሚ እየበለጸግን የምንገኝበት ደረጃ ላይ ስለሆንን ለእኛ ለዚህ ደረጃ መድረስ አስተዋጽ ላዳረጉ ሁሉ ምስጋና ልናቀርብና ጥረታቸውን አጠናከረው እንዲቀጥሉ ልናበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡ በማስከተልም በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኙት ውጤቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ በተለይ ለመንግስት፣ ማኅበር በማቋቋም ትግሉን ሀ ብለው ለጀመሩት የማህበሩ መሥራች አባላት፣ በየጊዜው የትግሉን ችቦ እየተቀባባሉ የበኩላቸውን ላደረጉት አመራሮች፣ ለአጋር ድርጅቶች፣ ለምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች፣ ከመስማት የተሳናቸው ጋር ለሚሠሩ ባለሙያዎች፣ ለመስማት የተሳናቸው ቤተሰቦችና ለመስማት የተሳናቸው ሁሉ በማኅበሩ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ገና ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎች መኖራቸው ጠቅሰው ሁሉም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት ታዳሚዎች በከፊል

በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት ታዳሚዎች በከፊል
(ፎቶ፡ ጳውሎስ ካሡ፣ ዶ/ር)

በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉደይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁን በመንግሥት በኩል የተሠሩ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን ዘርዝረው መንግሥት የተጀመሩ መልካም ጅምሮችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የመስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያን መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በምላሻቸው ውስጥ መስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያን መብቶቻቸውን ከመጠየቅ ጎን ለጎን ለተገኙ ውጤቶችም ዕውቅና አንዲሰጡና የመንግሥትን ጥረትም እንዲያበረቱ ጠይቀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የመስማት የተሳናቸው የኪነጥበብ ቡድን በምልክት ቋንቋ ጣዕም ያላቸው የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቅረብ ታዳሚውን እያዝናኑ አስተምረዋል፡፡ የበዓሉ አበይት ክንውኖች አንዱ የሆነው የማኅበሩን አዲስ ድረገጽ ምረቃ ነበር፡፡ ድረገጹ ተመርቆ ይፋ ተደርጓል፡፡ http://www.enadet.org የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጳውሎስ ካሡ (ዶ/ር) ድረገጹ በማኅበሩ አንጋፋ አባል በአቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ ያለምንም ክፍያ የተዘጋጀ መሆኑን በሂደቱ ላይ ሌሎች የማኅበሩ አባላት በምክርና በአርታኢነት መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡ ሥራው የተጀመረው በአቶ አበበ ታምራት አመራር ወቅት ሲሆነ ከአቶ አበበ ቀጥሎ አመራሩን የተረከቡት አቶ ቶፊክ ሐምዲኑር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ተገልቷል፡፡ በኤዲቶርያል ኮሚቴ አባልነት በማገልገል ለፕሮጄክቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላዳረጉት ለአቶ ተስፋዬ ገድሉ፣ አቶ ዓለሙ ወርቁ፣ አቶ አማረ አያሌው፣ ዶ/ር ጳውሎስ ካሡ፣ አቶ ባዬ ኢያሱና ወ/ት ኤልሳቤት መሸሻ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ተክለሃይማኖት ድረገጹን በኢንተርኔት ለመልቀቅ enadet.org ለሚለውን ስም የሚከፈለውን ወጪ የሽፈነውን በጎ ፍቃደኛም በማፈላለግ ትልቅ ድጋፍ በማድረጋቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አባላት በድረገጹ ላይ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ካዩ ሊጠቁሙ እንደሚችሉ ማኅበሩም ግድፈቶች ካሉ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ወደ ፊትም አዳዲስ መረጃዎች የሚጫኑ ሲሆን አባላት መረጃዎችን መላክ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ማኅበሩ በቀጣይ ሊሠራቸው ያቀዳቸው ብዙ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው አባላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሩ አቅርበዋል፡፡ በዕለቱ ከሰሜን አሜሪካ የመጡ የማኅበሩ የቀድሞ አባል ወ/ሮ እቴነሽ አየለ የኮረና ስርጭትን ለመከላል የሚረዱ ቁሳቁሶችን የለገሱ ሲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የመስማት የተሳናቸው ሳምንት 2014 ዓ.ም. ክብረ በዓል