ዶ/ር ሊዛ ኮፒነን ኢመየብማን ኅዳር 2008 ዓ.ም. ጎበኙ።

ሰኔ 19 ቀን 2009 - የኢመየብማ ባልደረባ

የ133 አገራት መስማት የተሳናቸው ማኅበራት የሚያገናኘው የዓለም መስማት የተሳናቸው ፈደሬሽን (ዓመየፈ) የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሊዛ ኪፒነን ኅዳር 2008 ዓ.ም. ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢመየብማ ጽሕፈት ቤት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። ወ/ት ሰሲሊያ ሃኒኮስኪ ከፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የወጣቶች ዘርፍ እና በአሰልጣኝነት ምክንያት ኢመየብማን አዘውትረው የሚጎበኙት የዛምቢያዋ ወ/ሮ ዩፍሬሲያ ምበዌ አብረዋቸው መጥተዋል።

ዶ/ር ሊዛ ኮፒነን ኢመየብማ ጠንካራ እንዲሆን የማድረጉ አስፈላጊነት
አስመልክተው ለአባሎች ምክር አዘል ንግግር አድርገዋል።
(ቪዲዮ፡ በተክለ ደርሶ)

ዶ/ር ሊዛ ኮፒነን ለኢትዮጵያ አዲስ አይደሉም። ከዚህ በፊት ከአንድ ጊዜ በላይ መጥተው ያውቃሉ። ሁለተኛው የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ክፍለ አህጉር የምልክት ቋንቋ ሴሚናር ዝግጅት በተደረገበት በ1982 ዓ.ም. እና በተጨማሪም በሴሚናሩ በተካሄደበት ሚያዝያ 1983 ዓ.ም መጥተው ነበር። የአሁኑ ጉብኝታቸው ልዩ የሚያደርገው የኢመየብማ የ2007 ዓ.ም. ባጀት ዓመት ጠቅላላ ጉባኤው ከሚደረግበት ጊዜ በመገጣጠሙ ነው። ኅዳር 18 -19 ቀን 2007 ዓ,ም. በተደረገውን የሁለት ቀናት ጉባኤው ተሳተፈዋል። አባሎቻችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅ ከሆኑ የመስማት የተሳናቸው መብቶች ተሟጋች እና ሥራቸውም በተባበሩት መንግሥታት እውቅና አግኝቶ የ2005/2006 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ሽፈልማት ተሸላሚ እንዲሆኑ ከተደረጉት ጋር ተገናኝተው ምክር ለማግኘት በመቻላቸው መልካም ዕድል ሆኖላቸዋል።

የተከበሩ እንግዶቻችን ዶ/ር ሊዛ ኮፒነን፣ ወ/ሮ ዩፍሬሲያ ምበዌ እና ወ/ሪት ሰሲሊያ ሃኒኮሲ በኢመየብማ ጠቅላላ ጉባኤ
    ኅዳር 18 -19 ቀን 2008 ዓ.ም.

የተከበሩ እንግዶቻችን ዶ/ር ሊዛ ኮፒነን፣
ወ/ሮ ዩፍሬሲያ ምበዌ እና ወ/ሪት ሰሲሊያ ሃኒኮሲ
በኢመየብማ ጠቅላላ ጉባኤ ኅዳር 18 - 19 ቀን 2008 ዓ.ም.
(ፎቶ፡ ተክለ ደርሶ)

ኢመየብማ በኢትዮጵያ፣ አፍሪካና በዓለም በሙሉ ላሉት መስማት የተሳናቸው ሁሉ ጠንካራ ደጋፊና ወዳጅ በመሆናቸው ዶ/ር ሊዛ ኮፒነንን ለማመስገን ይወዳል። ላደረጉት ያልተቆጠበ ጥረት ምስጋና ይደረሳቸውና በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት መፀደቀን ጨምሮ ብዙ በጎ ነገሮች ተከናውነዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በመስማት የተሳናቸው ሕይወት ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብለን ተስፋ ያደረግንበትን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት በማፅደቁ ኢመየብማ በጣም ተደስቷል።